1 ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው።
2 አክዓብም ናቡቴን፦ በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው።
3 ናቡቴም አክዓብን፦ የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው።
4 ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ። የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም።
5 ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ። ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው።
6 እርሱም፦ ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፦ የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት እርሱ ግን፦ የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት።
7 ሚስቱም ኤልዛቤል። አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ እንጀራም ብላ፥ ልብህም ደስ ይበላት የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ አለችው።
8 በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች።
9 በደብዳቤውም። ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት
10 ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች።
11 በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ።
12 የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት።
13 ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት !
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ